1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን የተማሪዎች ጥያቄ

ሰኞ፣ ግንቦት 5 2016

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን በሚል ባለፈው ዓመት በተመሰረተው ዞን ጎሮ ዶላ ወረዳ የብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ያለበቂ ዝግጅት ለፈተና እንድቀመጡ መጠየቃቸውን ገለጹ።

https://p.dw.com/p/4fnWa
 ፎቶ ከማኅደር፤ ምዕራብ ሸዋ ኦሮሚያ
ኦሮሚያ ክልል መልክአ ምድራዊ ገጽታ ፎቶ ከማኅደር፤ ምዕራብ ሸዋ ኦሮሚያ ምስል Seyoum Getu/DW

የተማሪዎች ጥያቄና ስጋት

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን በሚል ባለፈው ዓመት በተመሰረተው ዞንጎሮ ዶላ ወረዳየብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ያለበቂ ዝግጅት ለፈተና እንድቀመጡ መጠየቃቸውን ገለጹ።

የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎቹ በዚህ ዓመት በአዲሱ ዞን መዋቅር ተቃውሞ ምክንያት ትምህርታቸውን ባግባቡ መከታተል አለመቻላቸውን አመልክተው፤ ነገር ግን በዚህ አንድ ወር ውስጥ ይሰጣል ተብሎ በሚጠበቀው ብሔራዊ ፈተና ላይ ሊቀመጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት በበኩሉ በወረዳው የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተናዎቹን እንዲፈተኑ ሥራ እየተሠራ ቢሆንም በዓመቱ ትምህርታቸውን በበቂ ሁኔታ ያልተከታተሉ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ግን ብሔራዊ ፈተናውን አይወስዱም ይላል።

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተማሪዎች ጥያቄ

ዋቆ በሪሶ በምሥራቅ ቦረና ዞን ጎሮዶላ ወረዳ በሀርቀሎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ መሆኑን ይናገራል፡፡ ተማሪው በዚህ ዓመት በወረዳው በተከሰተው የዞን መዋቅር ተቃውሞ ምክንያት የ2016 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ጨርሶ አለመከታተሉን ያስረዳል።  

ሌላኛው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ኖቴ ቱራ ደግሞ በወረዳው ባሉ አራት 12ኛ ክፍልን በሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ሁሉ ምንም አይነት ትምህርት በዚህ ዓመት ባይሰጥም ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እንድንዘጋጅ ተጠይቀናል ይላል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የተማሪዎች ተምሳሌታዊ ማሳያ
ተማሪዎቹ በጸጥታ ችግር ምክንያት በተከታታይ የመማር ዕድል እንዳልነበራቸው ይናገራሉ። ፎቶ ከማኅደር፤ የተማሪዎች ተምሳሌታዊ ማሳያ ምስል Pond5 Images/imago images

  የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ስጋት

ከ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በተጨማሪ የ8ኛ እና 6ኛ ክፍል ተማሪዎችም ለብሔራዊ ፈተናው እንዲዘጋጁ እንደተነገራቸው ያስረዳሉ፡፡ በጎሮዶላ ወረዳየሀርቀሎ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ቦሩ ዱጎ በዚህ ዓመት ወደ ክፍል ገብተው ተማሪዎች የተማሩበት አጋጣሚ ባይኖርም ለፈተናው ግን እንዲዘጋጁ እንደተነገራቸው ነው የገለጸው። «አሁን ተፈተኑ እየተባለ ነው፡፡ ግን እኛ አልተማርንም፡፡ የነበረው የጸጥታ ሁኔታ ጥሩ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ አልተማርንም፡፡ እንዴት ሳንማር ለፈተና ተቀመጡ እንባላለን በሚል ትልቅ ቅሬታ ነው ያለን።» ነው የሚለው ተማሪው።

በዚሁ ወረዳ የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎችም ተመሳሳይ ስጋታቸውን ያነሳሉ። በወረዳው ከተማ ሀርቀሎ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ቢፍቱ ጎሮም በዓመቱ በዚህ ደረጃ የተሰጠው ትምህርት ውስን ቢሆንም ለፈተና እንዲዘጋጁ እንደተነገራቸው አስረድታለች።

የተማሪዎቹን ቅሬታ በተመለከተ ዶቼ ቬለ ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ባለሥልጣናት እና ለወረዳው አመራሮች በመደወል አስተያየታቸውን ለመቀበል ብርቱ ጥረት ቢያደርግም አልሰመረም። እንዲያም ሆኖ የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሤ ዋቆ በዚህ ዓመት የተስተጓጎለውን የትምህርት አሰጣጥ ሂደት ተከትሎ ለ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች እንጂ በወረዳው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለብሔራዊ ፈተና የማዘጋጀት እቅድ አለመኖሩን በአጭሩ አስረድተዋል፡፡ «የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ዘግየት ብለው ትምህርት ቢጀምሩም ትምህርት ከተጀመረ በኋላ ግን በመልካም ሁኔታ እየተሄደበት ነው» ያሉት ኃላፊውት ሌሎች ማብራሪያዎችን ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ምሥራቅ ቦረና ብሎ በአዲስ ባዋቀረው ዞን ውስጥ የምሥራቅ ጉጂ ውስን ዞኖችን በዚሁ ማካተቱ ተቃውሞን ሲያስነሳ የጎሮዶላ ወረዳ በዚሁ ተጠቃሽ እና ሰፊ ተቃውሞ የተስተናገደበት መሆኑ ይታወሳል።

 ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ